የማለዳ ወግ . . . አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ የተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች ጥሪ . . .

ነቢዩ ሲራክ: ECADF

አሮጌው የፈረንጆች አመት አልፎ በአዲስ አመት ከመግባቱ አስቀድሞ በዋዜማው ያየን የሰማነው በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩት የኮንትራት ሰራተኞች ውሎ አዳር ደስ አይልም ፡፡ በያዝነው ወርማ በተለያዩ የሳውዲ ጋዜጦች ሳይቀር የተዘመተብን ይመስላል ፡፡ የኮንትራት ሰራተኞች ተከላካይ ጠበቃ አጥተው ፤ በአሰሪዎች ሲባረሩ ፤ ሲደፈሩና አደጋው በርታ ሲል ተፍተው በኢንባሲና በቆንስል መስሪያ ቤቶች ጥገኝነት ይጠይቃሉ፡፡ ግፉአን ፍትህ ተነፍጓቸው ሲንገላቱ፤ ሲያብዱ ሲታመሙና በሃይል እርምጃ ነፍሳቸው ስትጠፋ ለመክረማቸው ምስክሮች ብዙ ነን ! እርግጥ ነው ለነፍስ ግድያ ተይዘውና ተወንጅለው ዘብጥያ የወረዱ እህቶችም አሉን ፡፡ የማለዳ ወግ . . . አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ የተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች ጥሪ

ወንጀሉና ግድያውን በምን ሰበብ አስባብ እንደፈጸሙት ግን ለእኛ የሚነግረን ፤ ለዜጎች ጠበቃ ሆኖ የሚሰማቸውና የሚከራከላቸው ያገኙ አይመስሉም፡፡ በእድሜ ያልበሰሉት እህቶች ነፍስ ለማጥፋት ያደረሳቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ሳይሆን ለመረዳት በመጠለያ ያሉ እህቶች ማነጋገር ይበቃ ይመስለኛል፡፡ እህቶች ተፈጸመብን የሚሉትን ግፍና የመደፈር ጥቃት አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ለመፈጸም የሚሰጥ ምክንያት ሊሆንና ወንጀልን መፈጸም አይገባም፡፡ ያም ሆኖ ሊገል የመጣን ገዳይ ለመከላከል አስበውትም ሆነ ሳያስቡት መግደል ራስን ከጥቃት ለመከላከል የሚደረግ እንቅስቃሴ እርምጃ መሆኑን ከህግ አንጻር የሚያስረዳ የመንግስት ተወካይ ያስፈልገናል፡፡

እንደ ዜጋ የተበዳዮችን ህመምና በደል ” እህ ” ብለን በማድመጥ ህግና ስርአትን ተከትለን መፍትሔ ልናፈላልግ ይገባል፡፡ ከምኖበት የቅርብ ርቀት ተፈጽሞ ግርግሩን በወቅቱ ዜናውን በጋዜጦች አንብቤያለሁ ! “ገደሉ” የሚባለውን ያህልም ባይሆን “ተገደሉ ” የሚለው አይነገርም ! ሲላቸው ራሳቸውን በራሳቸው አጠፉ ይሉና ” ሬሳቸውን ውሰዱ!” ይሉናል ! ለምን ራሳቸውን ገደሉ ብሎ ማን ይጠይቅልን ? !ራሳቸው ገደሉ እንኳ ቢባል ሌላን ሰው ከመግደል ራስን መግደል የመክበዱን ያህል ለዚህ ዜጎቻችን ለዚህ ያደረሳቸው ምክንያቱ ምን ይሆን ብሎ የሚያጠይቅልን አጥተናል ! ይህ ሁሉ እየሆነ አንድ የሳውዲ ጋዜጣ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ይፋ ያደረገው ሰነድ በጂዳ በሁለት የግድያ ወንጀል ፤ በያንቡ በግድያ ፤ በአልዘልፊ በደቡብ የሃገሪቱ ጠረፍ ፤ በአፈር አልበጠል ፤ በመካ በረፋዕና በተለያዩ የገጠርና ትላልቅ ከተሞች ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች በከባድ የግድያና የመሳሰሉት ወንጀሎች እንደተያዙ አልመዲና የተባለው ጋዜጣ አትቷል፡፡

እንደ ጋዜጠኛነቴ የዜጎችን ጉዳይ ለመከታተልና መረጃ ለማግኘት ወደ ቆንስሉ ብቅ ባሉኩበት አጋጣሚ ወደ ግቢው ለመግባት ስሞክር ቁም ስቅሌን የሚያሳዩኝ የቆንስሉ ዘበኛ በክብር ጎበስ ብሎ ያስገባቸው የሳውዲ አል መዲና ጋዜጠኞች የጅዳ ቆስንል ሃላፊዎችን አነጋግረው ያወጡትን መረጃ ማንበብ ሆድ አያሞላም፡፡ ልተወው . . .ብቻ የሳውዲ ጋዜጦች የሌለብንን እየለጠፉ ነፍስ ማጥፋታችን አግንነው የኮንትራት ስርራተኛ እህቶቻችንን ነፍስ በስነ ስርአት አልበኛነት እየኮነኑ የስራት አልበኛ ዜጎቻቸው ጥፋትና አሰቃቂ አያያዝ አኩስሰው ስለ መግደል ሙቅ ውሃ መቸለሳቸው ሰፊ ዘገባን እየሰሩ ይነግሩን ይዘዋል !

ከሁሉ በፊት ለዛሬው ድጋሜ የማለዳ ወጌ መነሻ ስለሆነኝ አፋጣኝ ትኩረት ወደ ሚሻው ጉዳይ ላምራ ! ከቆስንሉ አዲስ መጠለያ በቅርቡ እንዲገቡ ከተደረጉት ውጭ ያሉት 16 ተፈናቃዮች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ያገኘኋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቆንስሉና ከዚህ በፊት በርካታ ተፈናቃዮች በነበሩበት “መዲናተል ሃጃጅ” ከሚባለው መጠለያ አከራዮች መካከል በክፍያ የተነሳው ውዝግብ እልባት ባለማግኘቱ እዚያው ተጠልለው የነበሩ እህቶቻችን ለከፋ መከራ መዳረጋቸውን እውነትነት ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ ችያለሁ ፡፡

በመጠለያው የሚገኙ 6 የዓዕምሮ ህሙማንና ጨምሮ አስር ያህል እህቶች ከአስር ቀናት በላይ መብራትና ውሃ ተቆርጦባቸው በበራሪ ተባዮች እየተነደፉ እየገፉት ያለው የለት ተለት ኑሮ ሊናገሩት ይከብዳል ሲሉ ምንጮቸ ምስክረናተቸውን ሰጥተውኛል. . . የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ለእኒህን ተፈናቃይ ግፉአን ነፍስ አድን ጥያቄ መልስ ሲሰጡ መስማት ናፍቆኛል ! እኔ እጽፋለሁ ! እናንተ አንብቡ ! የመንግስት ሃላፊዎቻችን አፋጣኝ ትኩረት ለሚሻው የተፈናቃይ የኮንትራት ጥሪ ጀሮ ሊሰጡ ይገባል ! ጀሮ ያለው ይስማ . . .

የመሰንበቻውን የተፈናቃይ ኮንትራት ስራተኞች ውሎ ተጽፎ የሚገለጽ ብቻ አይደለምና ለህዝብ መብት ማስጠበቅና ለሰብ አዊ መብት ማስከበር የቆመ የመንግስትም ሆነ ገለልተኛ አካል ካለ በቃል ከመናገር ምስሎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለሚያይ ለሚሰማ የችግሩን ክፋት ማሳየት ይችላሉና የጀመርኩትን እቀጥለዋለሁ ! በኮሚኒቲው አዳራሽ አጠገብ የተሰራችው ጠባብ መጠለያ የተጠለሉት ግፉአን እህቶች ቁጥር ወደ ሰላሳ ሲጠጋ አምስት ያህሉ ዓዕምሯቸው ተነክቷል ! . . .አንዷ ተረጋግጣ ጋዜጣ ስታነብና ከራሷ ጋር ስታወራ ፤ ሌላዋ ግቢውንና ካፍቴሪያውን እየገባች እየወጣች ትረብሻለች፤ ስላት ከግቢው መካከል ካለችው አደባባይ ቁጥጥ ብላ በመውጣት ትደንሳለች ፤ትጫወታለች . . .ከግቢው ወጥታ በአስፓልቱ መሃል ቆማ መኪና እንዲገጫት ስትታገልና ሲመልሷት ተመልክቻለሁ ! መናገር መጋገር የማትፈልገው ሌላዋ ዘርፈጥ ብላ ተቀምጣና ነሁልሳና በራሷ አለም የነጎደቸው እህት ልብን በሃዘን ትሰብራለች፡፡

በሌላኛው መጠለያ ያሉትን ጨምሮ ዓዕምሯቸው የተነካና ያበዱትን እህቶች ቁጥር ከአስር በላይ እየሆነ ሲመጣ ጤነኞችና ህሙማኑ በአንድ ላይ ባሉባት መጠለያ ያበዱት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ያላበዱት ለእብደት መዳረጋቸውንና እንባቸውን እያዘሩ የገለጹልኝ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ነው ፡፡ በሪያድ ያለውን ሁኔታ ያጫዎተኝ ወዳጀ ከጅዳው በከፋ ሁኔታ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ያመላክታል፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ስለ ዜጎች መብት ገፈፋ በመረጃ እየተደገፈ ሲነገር የሆነ ያልሆነውን መረጃ ከመስተት ተቆጥበው በትክክል በዜጎች ላይ ለሚደርሰውና በአስፈሪ ሁኔታ እየተጋረጥነው ያለውን ችግር ለመመከት ህዝብ ተጠርቶ የሚመክርበት መንገድ አለያም ማዕከላዊ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲረዳና በዚህ ረገድ እርምጃ እንዲወሰድ ጠንከር ያለ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥ ይገባል፡፡

አዲሱ አመት ነጋ ጠባ የምናነሳ የምንጥለው የኢዮጵያውያን መከራ የሚቀልበት ያደርገው ዘንድ ምኞቴ ደግሜ በመግለጽ የዛሬውን ወግ ላብቃ !

ቸር አሰማን !

ነቢዩ ሲራክ