The Dallas Declaration

\"COALITION--696x175\"

የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ጉባኤ መግለጫ

መስከረም 29,2010 (October 8,2017)

Unity is our Destiny

 

“አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ

ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ፤ የእምቧይ ካብ”

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ”

 

ባልፉት 26 ዓመታትና በተለይም ባለፉት ወራቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደርስበትን ግድያ፤ እስር፤ መፈናቀል፤ ስደትና ረሃብ ያሳሰባቸው ተቆርቋሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ተሰባስበው  ኢትዮጵያ ሃገራችን የተደቀነባትን እጅግ አስጊ የሆነ ስርዓት ወለድ አደጋ በጽሞና ሲመራመሩና የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲያፈላልጉ ቆይተዋል።ይህ አስቸኳይ እና አሳሳቢ ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠውና ሁሉም የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች (Stakeholders)፤ በተለይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ኃላፊነቱንና ባለቤትነቱን ተቀብለው እንዲረባረቡበት ለማድረግ ያስገደደን ዋና ምክንያት የሰብአዊ መብቶች መረገጥና በኦሮምያ፤ በአማራ፤ በኮንሶና በሌሎች አካባቢዎች የሚካሄደው ህዝባዊ አመጽና ዐመጹን ለማቆም ህወሓት የሚወሰደው፤እርምጃ ከ1,000 በላይ የሚገመት፤ በአብዛኛው የወጣት ኢትዮጵያዊያን መጨፍጨፉ፤ በብዙ ሽህ የሚገመት ሰላማዊ ሕዝብ መታሰሩና እንዲሰወር መደረጉና ሀገሪቱም እንደሀገር ለመቀጠል ፈታኝ ሁኔታ ላይ መገኘቷ ነው። ይህ ጭካኔ የተሞላበትና ኢ-ሰብአዊ የኃይል እርምጃ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ሕግ የተከለከለ ነው።ዛሬ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ብዛት በአገራችን ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።

በአሁኑ ወቅት፤ በወንድማማቹ በኦሮሞውና በሶማሌው ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን መካከል የሚካሄደው የእርስ በርስ ግጭትና የሕዝብ መፈናቀል የህወሓት/ኢህአዴግ ብሔር-ተኮር ፖለቲካና በጎሳ ላይ የተመሰረተ የፌደራል አገዛዝ  ውጤት ነው። አገዛዙም አገሪቱን ለማስተዳደር ብቃት እንደሌለውም በጉልህ የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታ ሊቀጥል አይችልም። የኢትዮጵያና የ105 ሚሊየን ዜጎቿ መስረታዊ ችግሮች በተናጠል በሚካሄድ የተበታተነ ትግል ሊፈቱ እንደማይችሉ ካለፈው ተመክሯቸን ሰለተማርን የማህበራሰባዊው ድርጅቶች አስተባባሪ ኮሚቴ በመላው ዓለም የተመዘገበ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ተገናኝተው እንዲመካከሩና እንዲተባበሩ ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል።

በዚህም መሰረት ከመስከረም 27 እስከ 28 ድረስ በዳላስ ከተማ በተካሄደው የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ተወካዮች ጉባኤ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ በአበይት የአገር ጉዳዮች ላይ  ከጋራ ስምምነት ለመድረስ ተችሏል። አስኳሎቹም የሚከተሉት ናቸው።

  1. የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁኑ የአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሳዊ ስርዓት መሸጋገር እንዳለበት በማመን፤ ለዚህም ሽግግር መሳካት ብሄራዊ የሆነ የዓላማ አንድነት ስለሚያስፈልግ፤ ለውይይት የሚያገለግል መሰረታዊ ሰነድ (Framework) ስለተረቀቀና ለውይይት በሚረዳ መልኩ ስለቀረበ፤ ጉባዔው ሰነዱን መርምሮና አሻሽሎ  ለባለድርሻዎች ጉባዔ እንዲቀርብ ወስኗል።
  1. የማህበረሰባዊ ድርጅቶቹ ሰፊ ውይይት አድርገው የጋራ እሴት በሆኑት በኢትዮጵያ ቀጣይነትና ሉዐላዊነት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና በዜጎቿ እኩልነት፤ በሕግ የበላይነት፤ በሰብአዊ መብቶች መከበር እና በዲሞክራሳዊ ስርዓት አስፈላጊነት የማያወላውል የጋራ አቋም እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
  1. የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ከላይ ለተጠቀሰው የጋራ ብሄራዊ ዓላማ ስኬታማነት በመተባበር ድርሻቸውን የመወጣት ግዴታ እንዳለባቸው በማመን እንቅስቃሴያቸውን በጋራ አጠናክሮ ለመምራት የሚያስችላቸው የትብብር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
  1. ለማህበረሰባዊና ለፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለእምነት ተቋማት እና ለምሁራን ተሳትፎ እንዲጠቅም እና የጋራ ራዕይ ለማጎልበት እንዲረዳ የተዘጋጀው የዜጎች መብት የቃል ኪዳን ሰነድ (Citizens Charter/ Bill of Rights) ውይይት ተደርጎበት ጉባዔው ተቀብሎታል።
  1. በቃል ኪዳን እና በመሠረታዊ ሰነዱ የተጠቀሰው የግለሰብ፤ የዜጎች ሙሉ መብትና ተሳትፎ መከበርና ተቋማዊ መሆን ለዲሞክራሲ ስርአት መመስረትም ሆነ ቀጣይነት አስተማማኝ መመሪያ ከመሆኑም በላይ የቡድን መብቶችን መከበር በምንም መልኩ የማይጻረር መሆኑንና ሰነዱን ማዘጋጀት ብዙ ምሁራንና ባለሞያዎች የተሳተፉበት መሆኑን በመገንዘብ፤ ጉባዔው ተወያይቶ ተቀብሎታል።
  1. የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ተወካዮች በውይይት ከደረሱባቸው ግንዛቤዎችና ውሳኔዎች መካከል አንዱ የተበታተነው ጥረታቸው አመርቂ ውጤት ለማስገኘት ባለመቻሉ ለጋራ ብሄራዊ አላማ እየተጋገዙ አቅምን ማጎልበት አስፈላጊ እና ወሳኝ መሆኑ ነው።
  1. በመሆኑም፤ የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች የሆኑ የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ባንድ ድንኳን ውስጥ(One Inclusive Tent) ለመሰባሰብ፤ ለመረዳዳት፤ አብሮና ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል መግባቢያ ሰነድ፤ ተፈራርመው መዋቅርና አመራር እንዲኖር(Consortium) “የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር”ን በመመስረት ፤ በመዋቅሩ፤ በአመራሩና በወደፊት የስራ ትኩረቱ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
  1. የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር ዋና ዓላማና ግብ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን እና የሕዝቡ አይነተኛ ጥያቄ የሆነውን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመሸጋገሩን ሂደት ለማፋጠን፤ ሁሉም ባለድርሻ የሆኑ ድርጅቶች፤ ተቋሞችና ግለሰቦች እንዲተባበሩ ለማድረግ፤ የእውቀት፤ የመረጃ፤ የአቤቱታ፤ የገንዘብ፤ የዜና ስርጭት፤ ተመሳሳይና ተደጋጋፊ አቅምን ለማጠናከር እንዲሆን ጉባዔው ተስማምቶበታል።
  1. የማበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቀራረብ አስፈላጊነት እና ወሳኝ ሚና በማጤን የሚመለከታቸው ሁሉ ለትብብሩ መጠናከር እና ስኬታማነት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት ለማበረታታት፤ ለመጎትጎት እና የተጠናከረ ክትትል ለማድረግ ወስኗል።
  1. በማህበረሰባዊ ድርጅቶች ምስረታ እስካሁን ያልተሳተፉ እና ተመሳሳይ አላማ ያላቸው ድርጅቶች የትብብሩን መርሆዎች እና አላማዎች ተቀብለው እንዲሳተፉ ጉባዔው ወገናዊ ጥሪ ያቀርባል።

ኢትዮጵያዊነት እና የዜጎቿ አንድነት ይለመልማል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተባበረ ክንዱ መብቱን እና ሉዐላዊነቱን ያስከብራል።